ብርሃነ ልደቱ ለእግዚእነ
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ
“ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃን ዓቢየ ወለአለሂ ይነብሩ ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ብርሃን ሠረቀ ሎሙ”
ብርሃነ ልደቱ ለእግዚእነ
በድንቁርናና በቀቢጸ ተስፋ ለነበሩ ሰዎች ፍጹም እውቀት ተሰጣቸው፤ ሞት ባመጣው ምስል ሞትን በመምሰል ለነበሩ ሰዎች ክርስቶስ ተወለደላቸው በሞተ ሥጋ በሞተ ነፍስ ለነበሩ ልጅነት ተሰጣቸው፤ በኃጢአት ለነበሩ ስርየት፤ በክህደት ለነበሩ ሃይማኖት ተሰጣቸው ኢሳ.ም 9፣2እግዚአብሔር የሁላችን አባት አዳምን በአርአያውና በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ባረከው ሁሉንም እንዲገዛ እንዲነዳ ሥልጣን ሰጠው፤ በረከቱን፣ ሥልጣኑንና ሲሳዩን ከሰጠው በኋላ ፈጣሪውን የሚያስታውስበት ትዕዛዝ አዘዘው፡፡ ትዕዛዙም የፈጣሪና የፍጡር መለያ፣ የአዛዥና የታዛዥ ገደብ፣ ሰው ለሕግ መገዛት እንደሚገባው ለማስረዳት የተደረገ እንጂ የስስት ወይም የንፍገት አልነበረም፡፡
ይህንን ደግሞ አዳምም ሆነ ሔዋን ያውቁታል፤ በምግብ እጦት እንዳይቸገሩ ግን በገነት ያሉትን አትክልት እንዲበሉ ከውኃውም እንዲጠጡ ፈቅዶላቸዋል፡፡ሰው ግን ከፍጥረት አክብሮ አልቆ ያነገሠውን እግዚአብሔርን አስቀይሞ በተሳሳተ ምክር ተመርቶ አትብላ የተባለውን ዕፀበለስን ስለበላ ከፈጣሪውም ትዕዛዝ ስለወጣ በዚህ ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡
