Thursday, July 12, 2012

መልክዐ ተክለ ሃይማኖት ሰላም ለፅንሰትከ


   ክፍል ሁለት   መልክዐ ተክለ ሃይማኖት  ሰላም ለፅንሰትከ
             "ሰላም ለፅንሰትከ ወለልደትከ እምከርሥ።አመ ዕሥራ ውረቡዑ ለወርኃ ታኅሣሥ።ተክለሃይማኖት በኩሉ ወበውስተ ኰሉውዱስ ።ናሁ ወጠንኩ ወዕቤ ለስብሓቲከ ሐዲስ ።በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ።"ትርጉም ''ተክለ ሃይማኖት ሆይ አስቀድሞ በማህጸንለተጸነስከው ጽንሰትህና በታህሳስ ሃያ ዐራት ቀን ለተወለድከው መወለድህም ሰላም እላለው በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ ተክለሃይማኖት ሆይ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብዬ አዲስ የሚሆን ምስጋናህን እጀምራለሁ''በክፍል አንድ ጽሑፋችን '' ሰላም ለፅንሰትከ ወለልደትከ እምከርሥ። 

       አመ ዕሥራ ውረቡዑ ለወርኃ ታኅሣሥ።''የሚለውን የአባታችንን ፅንሰታቸውን እና ልደታቸውን የሚያወድሰውን ክፍል ተመልክተን ነበር በዚህ ጽሁፋችን ደግሞ'' ተክለሃይማኖት በኩሉ ወበውስተ ኰሉውዱስ  ናሁ ወጠንኩ ወዕቤ ለስብሓቲከ ሐዲስ  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ።"ትርጉም  '' በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ ተክለሃይማኖት ሆይ  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብዬ አዲስ  የሚሆን ምስጋናህን እጀምራለሁ''
               በቅድስት ቤተክርስትያን ስርአት መሰረት የማንኛውም ተግባር መጀመርያ ስመ ስላሴን መጥራት ነው የምታድርጉትን ሁሉ በጌታ ስም አድርጉት ስለተባለ የጸሎትም መጀመርያ በስላሴ ስም ማማተብ ነው ምእምናን ጸጋ የሚያግኙበት የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበት ምስጢረ ጥምቀተት እንኳን የሚፈጸመው በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ማቴ ፳፰፤፲፱ ለዚህም ነው የአባታችን ምልክዐ ጸሎታቸው ሲጀመር በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ የተባለው ይህም እያንዳንዱ ክርስትያን የግልም ሆነ የማህበር ጸሎት ሲያደርግ በስላሴ ስም ማማተብ እንዲገባ ያስተምረናል ጌታም በወንጌል እንዲህ ብሎ ነግሮናል
«ወደ አብ እሄዳለውና አብም ስለወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እኔ አደርገዋለሁ» ዮሐ ፲፬፡፲፫ በተጨማሪም«በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ እኔም ስለናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም»ዮሐ፲፮፡፪፮
                  በስሜ የምትለምኑትን ማለት በስመ ተወላዲ አምናችሁ ወልድን ተወላዲ ብላችሁ በስመ ወላዲ አምናችሁ አብን ወላዲ ብላችሁ በስመ ሰራጺ አምናችሁ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብላችሁ የምትለምኑትን እኔ አደርገዋለው በማለት በስልጣን ከአባቱ ከአብ ከሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል መሆኑንም ጭምር አስግንዝቦአል እንግዲህ የቅዱስ አባታችን መልክዐ ጸሎታቸው በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ተብሎ መጀመሩ መጽሐፍ ቅዱስን ምሰረት ያደረገ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። በሁሉ ዘንድ    የተመሰገንክ ቅዱሳን በሁሉ ዘንድ የከበሩ የተመሰገኑ እንደሆኑ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምረናል በሁሉ ዘንድ ማለት በሰዎች በመላዕከትእና በእግዚአብሔር ዘንድ ማለት ነው እግዚአብሔር አምላካችን ለቅዱሳኑ ከሚሰጣቸው ጸጋ አንዱ በሁሉ ዘንድ መወደድ መፈራት፤ ግርማ ሞገስ እና በጸጋ መመስገን ነው ይህንንም ለመረዳት የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መመልከት ይቻላል
                  '' የሚባርኩህንም እባርካለው'' ዘፍ12ርዕሰ አበው ለሆነው ለአባታችን ለአብርሃም በተነገረው በዚህ ኃይለ ቃል እንደምንመለከተው ቅዱሳንን የሚባርክ የሚያመሰግን እርሱ እንደ ሚባረክ በረከተ ስጋ ወነፍስ እነደሚያገኝ ቅዱስ ቃሉ በግልጽ ያስቀምጣል ስለዚህም ከቅዱሳን አንዱ የሆኑትን አባታችንን ቅዱስ ተክለሃይማኖትን ማመስገን በረከተ ስጋ ወነፍስ የሚያሰጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው እንጂ  የስጋና የደም ትምህርት አይደለም። ዛሬ ማንም ተነስቶ የአባታችንን ቃል ኪዳን አማላጅነት ለማስተባበል ቢሞክር ፤የሚገባቸውንም የጸጋ ምስጋና ከማቅረብ ቸል ቢል ወይም የትዕቢት የጽርፈት ቃል ቢናገር ከሁሉ አስቀድሞ የሚጎዳው ራሱን ነው ምክንያቱም በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ተብሎ ስለተጻፈ ''የሚረግሙህንም እረግማለው'' ዘፍ123
            በተጨማሪም''ጻድቃንን የሚጠሉ ይጸጸታሉ ''መዝ3321 እንዲሁም ጌታ ራሱ በወንጌል'' እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል'' ሉቃ1016እንግዲህ በቅዱሳን ላይ የማይገባ የድፍረት ንግግር መናገር የእርግማን ፤የውድቀት እና የዘላለማዊ ጸጸት ውጤት ከሆነ አንዳንዶች ስለምን ወደዚህ ድፍረት ገቡበእርግጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ ''ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ስልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም''2ጴጥ211ብሎ እንደገለጸው ካደረባቸው መንፈሰ ጽርፈት ተነስተው የስድብ መሳርያ ቢሆኑ የሚደንቅ ነገር አይደለም። ለቅዱሳኑ ክብር የሚቆረቆር እግዚአብሔር ግን ዝም አይልም በቅዱሳኑ ላይ ስለምትሰነዘር እያንዳንዷ ቃል ይፈርዳል ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በኦሪት ዘኁልቁ ምዕራፍ ፲፪ የተዘገበው ታሪክ ነው የሙሴ ወንድም ካህኑ አሮን እና እህቱ ማርያም በታላቁ ነቢይ ሙሴ ላይ እንዲህ በማለት የድፍረት ቃል ተናግሩ «በእውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮልን ? በኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን አሉ» ዝኁ፲፪፡፪ይህንንም የሰማ እግዚአብሔር በጣም ተቆጣ ሶስቱንም ወደ ቤተመቅደሱ እንዲመጡ ከጠራቸው በኋላ በሚያስፈራ ግርማ በአምደ ደመና ወረደ ካህኑ አሮንንና እህቱ እንዲህ በማለት ተቆጣቸው «ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለውበምሳሌ አይደለም የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል በባርያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለምን አልፈራችሁም አለ» ዘኁ ፲፪፡፮  ወዲያውኑ ማርያም እህተ ሙሴ በለምጽ ነደደች አሮንም ካህን ስለንበር ከህዝባዊያኑ ጋር ቅጣቱ ስላልተገለጸ እንጂ ተቀጥቶአል እግዚአብሔር አምላክም መልሳቸውን እንኳን ሳይጠብቅ ትቶአቸው ሄደ አዎን ዛሬም በቅዱሳኑ ላይ ማንኛውንም አይነት የድፍረት ንግግር የሚናገሩ ተጸጽተው ንስሃ ካልገቡ ቅጣቱ የማይቀር ነው። ለጊዜው በሕይወተ ስጋ ሳሉ በክህደት ለምጽ ሲነዱ ይኖራሉ በኋላም ዘላለማዊ እሳት እንደ ለምጽ ሲበላቸው ይኖራል። እንግዲህ ምን እንላለን ለቅዱሳኑ የሚገባውን ክብር ከመስጠት ወደኋላ ብለን እግዚአብሔርን እናስቆጣውን ? አይደለም ተገቢውን ክብር ለወዳጆቹ እናቅርብ እንጂ። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጋ አባታችን ቅዱስ ተክለሃማኖትን በሁሉ ዘንድ የተመሰገንክ እያለች ታወድሳቸዋለች አዎን በእውነት አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖት በሁሉ ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው ለዚህም ገድል ትሩፋት የፈጸሙባት ምድረ ኢትዮጵያ ቋሚ ምስክር ናት የአባታችን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ሥራ በኢትዮጵያ ብቻ ያበራ አይደለም ታሪካቸውን መርምረው የተደመሙበት አውሮፓዊያን ሳይቀሩ በቤተ መዛግብቶቻቸው ከትበው አስቀምጠውታል
             በቃልኪዳናቸው የታመኑ ግብጻዊያን ክርስትያኖች እንኳን በስማችው ቤተክርስትያን አሳንጸው በረከታቸውን ይሳተፋሉ።በምድረ አሜሪካም ታላቅ የጸሎት ሰው ተብለው ሰዕላቸው በቤተመዛግብቶቻቸው ሳይቀር ተቀምጦል።ታዲያ እኚን የመሰሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ መገለጫ የሆኑ አባት በሁሉ ዘንድ የተመሰግኑ ቢባሉ በትክክል ቢገልጻቸው እንጂ ምን የሚያስተች ነገር አለው  ፡;
                          አምላከ ቅዱሳን  ጸጋውን ያብዛልን 
                                ወስብሐት ለእግዚአብሔር   
                                  ወለመስቀሉ ክቡር
                                  ወለወላዲቱ ድንግል
ከዚህ በፊት ያለውን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ /

No comments:

Post a Comment