Thursday, September 10, 2015

ዜና ህይወቱ ለድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳስ


                   የቤተክርስቲያን የቀን መቁጠሪያን ያዘጋጀ  ድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳስ  ነው!ድሜጥሮስ ማለት መስተዋት ማለት ነው፡፡ ሀገሩ እስክንድርያ ነው፡፡ አባት እናቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋጎች ነበሩ፡፡ ላባቱ ወንድም ሴት ልጅ ነበረችው ሲሞት ልጄን ከልጅህ አትለይብኝ ብሎት አብሮ አሳድጓቸዋል፡፡አካለ መጠን ሲያደርሱ ዘመኑ አረማውያን የበዙበት አማንያን ያነሱበት ነበርና ከሌላ ብናጋባቸው ከሃይማኖት ከገቢረ ሠናይ ይርቃሉ፤ ሕገ ነፍስ ከሚፈርስ ሕገ ሥጋ ይፍረስ ብለው አጋቧቸው፡፡ በልተው ከጠገቡ ጠጥተው ከረኩ በኋላ ሥርዓተ መርዓዊ ወመርዓት ያድርሱ ብለው መጋረጃ ጣሉባቸው፡፡ እሷ አስቀድማ ድሜጥሮስ ያንተ ወንድምነት ለኔ የእኔ እኅትነት ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አለችው፡፡ እኔስ የአባት የእናቴን ፈቃድ ልፈጽም ብዬ እንጂ ፈቃዴ አይደለም፤ በዚያውስ ላይ አንቺ ከፈቀድሽ ብንተወው እንችል የለምን? አላት እንተወው አለችው፡፡ እንኪያስ አንቺንም ለሌላ እኔንም ለሌላ እንዳያጋቡን መስለን እንኑር አላት፡፡ በዚህ ተስማምተው አንድ ምንጣፍ እያነጠፉ አንድ ዐጽፍ እየተገናጸፉ 48 ዘመን ኖሩ ፡፡ ምነውመኑ ይክል ሐቁረ. እሳት በሕጽኑ ይል የለምን እንደምን ይቻላል? ቢሉ ሕሩይ ለንጽሕና ነውና አንድም እሳቱን እንዲታፈኑ ማድረግ ለጌታ ይሳነዋልን? መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ቀኝ ክንፉን ለርሱ ግራ ክንፉን ለርሷ አልብሶ አድሮ ሲነጋ በአምሳለ ርግብ በመስኮት ወጥቶ ሲሄድ ያዩት ነበር፡፡

                   በዘመኑ የነበረ ሊቀጳጳስ ሉክዮስ /ሉክያኖስ/ ይባላል፣ አረጀ ደከመ፡፡ ሕዝቡን ሰብስቦ እኔ አርጅቻለሁና ከኔ ቀጥሎ የሚሾምላችሁን ምረጡ አላቸው፡፡     አባታችን አንተው ግብር ገብተህ ቀኖና ይዘህ ንገረን እንጂ እኛ ምን እናውቃለን አሉት፡፡ ቀን ቀጥሮ አሰናበታቸው፡፡ በቀጠራቸው ቀን ተሰበሰቡ በሱባኤው የታዘዘው መልአክ ነግሮት ነበርና ያለጊዜዋ ያፈራች አንዲት የወይን ዘለላ ይዞ ሊባረክ ከኔ ዘንድ ይመጣል ከኔ ቀጥሎ የሚሾም እርሱ ነው አላቸው፡፡ ወዲያውም ድሜጥሮስ ከሚስቱ ጋር ተማክሮ ከአጸደ ወይኑ ያገኛትን ያለ ጊዜያዋ ያፈራች አንዲት የወይን ዘለላ በሙዳይ ይዞ መጣ፡፡ የያዘውን አበርክቶ በረከት ተቀብሎ ሲወጣ፤ ከኔ ቀጥሎ የሚሾምላችሁ ይኸ ነው ብሎ አመለከታቸው፡፡
                      ሊቀ ጳጳሱም አልሰነበተም አረፈ፡፡ እርሱን ቀብረው ሲመለሱ መንበር ያለ ሹም አያድርምና ተሾምልን አሉት፡፡ ንጹህ ድንግል በሚቀመጥበት መንበር እንደኔ ያለ ሕጋዊ ያልተማረ ይሾምበታልን? ብሎ እምቢ አላቸው፡፡ አባታችን ነግሮናል ብለው ግድ አሉት እንኪያስ ሥርዓት አስተምሩኝ አላቸው፡፡ አልተማርኩም ስላልክ እንጂ አባታችንማ አንቀጸ ብፁአንን አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ተርጉሞ ነበር የተሾመው አሉት፡፡ እስኪ መጽሐፉን አምጡልኝ አላቸው፡፡ አመጡለት ንባቡ ከነ ትርጓሜው ተገልጾለት አንብቦ ተርጉሞ ተሹሟአል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ብሉያት ሐዲሳት ተገልፀውለታል፡፡   ኋላም ከፍጹምነቱ የተነሣ ቀድሶ ሲያቆርብ የነጻውና ያልነጻው፤ የበቃውና ያልበቃው እየታየው ተለይቶ አንተ በቅተኃል ተቀበል፤ አንተ አልበቃህም ንስሐ ገብተህ ከኃጥያት ነጽተህ ቅረብ የሚላቸው ሆነ፡፡ ብዙዎቹ እየፈሩ ኃጢአታቸውን ለመምህረ ንስሐቸው እየነገሩ መምህረ ንስሐቸው ያዘዝዋቸውን እየሠሩ እሚቀርቡ ሆነዋል፡፡ ሌሎች ግን ንጹሕ ድንግል በሚሾምበት በመንበረ ማርቆስ መቀመጡ አንሶት እንዲህ ይለናል ብለው አሙት፡፡ መልአኩ መጥቶ ድሜጥሮስ ኢትፍቅድ አድህኖ ርእስከ ባሕቲቱ አላ ክስት ዘሐሎ ምስሌከ ወማዕከለ ብእስቲከ የራስህን መዳን ብቻ አትሻ ህዝቡ በሐሜት ተጐድተዋልና በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ምሥጢር ግለጽላቸው አለው፡፡ 
                     በማግስቱ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነበር ቀድሶ ካቆረበ በኋላ እሙቅ እሳት አስነድዶ፤ ከውስጡ ገብቶ ሲጸልይ ቆይቶ፤ ሚሰቱን አስጠርቶ ስፍሒ አጽፈኪ. ልብስሽን ዘርጊ ብሎ ከፍሕሙ እየታፈነ በልብሷዋ ላይ አደረገላት ህዝቡን ሦስት ጊዜ ዞራ መልሳዋለች አባታችን ይህን ማድረግ ስለማድረግህ ስለምን ነው አሉት መልአኩ በሐሜት እንደተጐዳችሁ እና በሁለታችሁ መካከል ያለውን ምሥጢር እንድገልጽላችሁ ቢነግረኝ ነው፡፡ ይህን ያህል ዘመን አብረን ስንኖር በግብር አንተዋወቅም አላቸው ሥረይ ለነ አቡነ እስመ. ንሕነ አበሳነ ወጌገይነ በድለናል ይቅር በለን እያሉ ከእግሩ ወደቁ፡፡ ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይስረይ እግዚእነ ኢየሱስ ይቅር ይበላችሁ ያስተስርይላችሁ ብሎ ናዟቸዋል፡፡ ኑዛዜ የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
                   ከዘመነ.ሐዋርያት እስከርሱ ድረስ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ገዳመ. ቆሮንቶስ ገብቶ 40 ቀን 40 ሌት ጾሟል እያሉ ጥምቀትን ባከበሩ ማግስት ይጾሙ ትንሳኤን በዋለበተ ያከብሩ ነበር፡፡ እሱም ቢገልጽልኝና ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ ስቅለት ከዓርብ፤ ዕርገት ከሐሙስ ባይወጣ በወደድሁ እያለ ይመኝ ነበር፡፡ የሹትን መግለጽ ለመንፈስ ቅዱስ ልማድ ነውና ገልጾለት ባሕረ ሐሳብን ደርሷል፤ ጾመ ነነዌ፣ በዓተ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ ሆሣዕና፤ትንሣኤ፤ ጰራቅሊስ ከእሑድ ስቅለት ከዓርብ ፤ዕርገት ከሐሙስ እንዳይወጣ አድርጓል፡፡ ባረጀም ጊዜ በአልጋ ተሸክመው ቤተክርስቲያን እያደረሱት እስከ ዕርበተ. ፀሐይ ድረስ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ምን ቢጸድቁ ምን ቢበቁ ሥጋ ከለበሱ ዘንድ ሞት አይቀርምና በተወለደ 105 ዓመቱ ዐርፏል፡፡

No comments:

Post a Comment