Friday, July 6, 2012

መንፈሳዊውን ከመንፈሳዊው ጋር

     ሚልክያስ ማለት መልእክተኛዬ ማለት ነው:: ነቢዩ ሚልክያስ አራት ምዕራፎች ያሉት የትንቢት መጽሐፍ ጽፏል:: የነበረበት ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በነእዝራና ነህምያ ዘመን 470-440. መካከል ነው::በትንቢት መጽሐፉ ከጻፋቸው ነገሮች መካከል ስለ ቃል ኪዳን መልእክተኛው ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተናገረው ይገኝበታል::<<እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል . . . >> /ሚል.3:1/::
             ነቢዩ ስለቅዱሱ አባት ስለሰጠው ምስክርነት የሚወቅሰው ማንነው?ስለ ቅዱሳን መናገርን ስለ ቅዱሳን መጻፍንና መመስከርን ሀሰት የምትሉ እናንተ ሆይ ስንፍና ከምትወልደው ጥፋት ታመልጡ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ:: ከአበይት ነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስ <<የአዋጅ ነጋሪ ቃል>> በማለት የጠራው ማንን ነው? ነቢዩ ይህንን ስለማን ይናገረዋል? ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን አልተረዳህም? /ኢሳ.41:1/::ነቢያትን ስለምን የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ብቻ መርጣችሁ አልተናገራችሁም ብለን እንውቀሳቸውን? አይደለም:: እነርሱን መልእክተኛ አድርጎ የላከ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ የገለጠላቸውን ጻፉ:: መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር ስናነጻጽረው ስለ ቅዱሳን እንዲወሳ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ እንረዳለን እንጂ:: ስለ ብዙ ቅዱሳን ከመወለዳቸው በፊት በሕልም የታለመላቸው ከመወለዳቸው በፊት በነቢይ የተተነበየላቸው ከመወለዳቸው በፊት በመላእክት የተነገረላቸው ብዙ ናቸው::ዮሐንስ መጥምቅ አንዱ ማሳያ ነው::
                 ስለ ጻድቁ አባት የተነገረው በነቢያት ቃል ብቻ አይደለም:: እግዚአብሔር ለአንድ አገልግሎት የመረጠው የቃል ኪዳን መልእክተኛ የታጨ አገልጋይ ነውና የሚያውቁትና የሚመሰክሩለት የከበሩ ነቢያት ብቻ አይደሉም:: የእግዚአብሔር መላእክትም ጭምር እንጂ:: መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መጥምቁ ዮሐንስ እንደሚወለድ ብቻ ያበሰረ አይደለም:: ተልእኮው ሥልጣን ያለው ነውና የምሥራቹን የጠረጠረውን ካህኑ ዘካርያስን ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ ዲዳ ትሆናለህ ብሎታል:: ስለ መጥምቁ ሕይወትም ገልጦ ተናግሯል:: አስተዳደጉን አመጋገቡን ሁሉ አስረድቷል:: መልአኩ በዚህ ሁሉ ለምን ይደክማል? ድንቅ ነገር ይህ የከበረ መልአክ ደግሞ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ደግሞ የሚያበሥር ነው:: እንደ ጊዜ ግብሩ ስለቅዱሱ አባት ይናገር ዘንድ አያፍርም:: ወንጌላውያን ደግሞ የቅዱሱን አባት ገድል ነገረ ክርስቶስን ለመናገር መቅድም አደረጉት:: ስለ መንገድ ጠራጊው ሳንናገር ስለ ክርስቶስ ልንናገር እንዴት እንችላለን? ስለ ዮሐንስ መጥምቅ መናገር ስለ ክርስቶስ መመስከር ነው:: መጥምቁ ከጌታችን የተለየ ሕይወት አልነበረውም ከጽንሰቱ ጀምረን ስለ እርሱ ስንመሰክር የምንናገረው እግዚአብሔር በቅዱስ ዮሐንስ ሕይወት ስላደረገው ነው:: መንፈሳዊውን አባት ከመንፈሳዊው ገድለ ቅዱሳን ጋር ሲነጻጸር ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው::

        መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምን ብሎ መሰከረ? ስለቅዱሳን ዛሬ ስንመሰክር ምን ብለን ነው? ቅዱስ ገብርኤል እንደመሰከረው እንደተናገረውአድረገን አይይደለምን? <<ገና በእናቱ ማኅጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል >> ማለት ቅድስናውን መናገር ነው:: <<በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል>> <<ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል>> ብሎ አገልግሎቱን ነው የመሰከረው:: <<በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል>> ያለው መንፈሳዊውን አባት ከመንፈሳዊው ሰው ጋር ክብሩና ማእርጉን ለማንጸር ነው:: ስለ እግዚአብሔር ወዳጆች ስለ ቅዱሳን ስንናገር መልአኩ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ክብር ቅድስናና አገልግሎት እንደመሰከረው መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር በማስተያየት ነው:: ጻድቁ አባት ገበረ መንፈስ ቅዱስ በናታቸው እቅፍ አመሰገኑ ቅዱስ ዮሐንስ በናቱ ማኅጸን ዘለለ ልዩነቱ የቱ ጋር ነው? የማኅጸን ሽል የሰገደው ለእርሱ ነው:: የዕለት ውልድ ያመሰገነውም እርሱን ነው:: የጠፋው ግን እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም የሚል እምነት ነው:: የሃይማኖት ምስክርነት በሥጋ እውቀት ብቻ አይሆንም:: ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መቃኘት ያስፈልገዋል:: ስለ ቅዱሳን መመስከር አንዱ የሃይማኖት ምስክርነት ነውና ካህኑ ዘካርያስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ሲሰጥ የተናገረው ስለ ሥጋ ልጁ ብቻ አይደለም:: ምስክርነቱ የመንፈስ ቅዱስ ነው::/ሉቃ.1:67/::
                        ካህኑ ዘካርያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሲመሰክር ሁለት ነገሮች ቀድመውታል:: የመጀመሪያው የመልአኩን ቃል ባለመቀበል ዲዳ ሆኖ መቆየቱና ሲከፈት የመጀመሪያ ሥራው ስለ ጻድቁ መመስከሩ ሲሆን:: ሁለተኛው ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ መናገሩ ነው:: እምነትን እንደተሰበከላቸው የማይቀበሉ ሰዎች ሁሌም የሚገጥማቸው ምን እንደሆነና ስለ ቅዱሳን መመስከር የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ካልሆነ በቀር የማይቻል መሆኑን የካህኑ ሕይወት ምስክራችን ነው:: በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ስለ ቅዱሱ አባት <<ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤>> ብሎ መናገር የሚችል ማን ነው? መንፈሳዊ ቤተሰብ እንዲህ ለቅዱሳን ምስክርነት ሲሰጥ የሚኖር ነው:: ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እመቤታችንን አመሰገነች: ባሏ ካህኑ ዘካርያስ በመንፈስ ተሞልቶ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስን አከበረ:: መንፈሳዊው ነገር ከመንፈሳዊው ጋር ሲነጻጸር እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ ተብሎ የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ያደረጉትን ከማድረግ የሚልቅ ቅድስና ከየት አለ? በፍኖተ ቅዱሳን ነው የምንሄደው ስንል እንደነሱ እያመሰገንን ነው የምንኖረው ማለታችን ነው::

            ለቅዱሳን ምስክርነት የምንሰጠው በቃል ብቻ አይደለም:: ሕይወታቸውን የሚዘክር የሚናገር ገድል ይጻፍላቸዋል እንጂ:: ገድለ ቅዱሳንን መጻፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ቀጣይ ታሪክ መጻፍ ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀ መጽሐፍ አይደለም:: በይዘቱም የበርካታ ቅዱሳን ገድል /ልደት እድገት አገልግሎት እረፍት ቃል ኪዳን/ በውስጡ ይዟል:: ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ገድላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው:: አራቱም ወንጌላውያን ስለ ጻድቁ አባት ተባብረው መስክረዋል:: ለምን ይላቸው ዘንድ የሚደፍር ይኖር እንደሆነ ሳስብ ይደንቀኛል:: የመንፈስ ቅዱስን አሳብ እያረመ ሊቀበል የሚወድ ፈሪሳዊ ልብ ነውና:: ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምነን፥ በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ በጻፉልን የሕይወት መጽሐፍ ውስጥም ገድለ ቅዱሳን ተጽፏል። ወንጌላውያን ገድለ ዮሐንስን ለመጻፍ ምንአተጋቸው?ባለቃል ኪዳን አገልጋይ ነዋ መጥምቁ:: ሊመሰከርለት ሊጻፍለት ይገባ ነበርና ጻፉ:: መንፈሳዊው ነገር ከመንፈሳዊው ጋር ሲተያይ ለገድለኛ ቅዱሳን ለምንጽፈው ገድል ሁሉ መሠረቱ ወንጌል መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው:: አራቱም ወንጌላውያን ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ሲመሰክሩ በነቢያት የተነገረለት እርሱ እንደሆነ አረጋግጠው ጽፈዋል:: /ማቴ.3:3 ማር.1:2-3 ሉቃ.3:3-6/::

      ወንጌላዊው ሉቃስ ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በቂ መረጃ የሰጠን ወንጌላዊ ነው:: እናትና አባቱ ማን እንደሚባሉ:: ሕይወታቸው ምን ይመስል እንደነበር አገልግሎታቸውን ወገናቸው ከወዴት እንደሆነ ጽፏል የመጥምቁ ኑሮም በበረሀ እንደነበር መስክሯል::/ሉቃ.1:/:: ሐዋርያው ማቴዎስም አቋሙን ሲገልጽ <<ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።>>ብሏል:: አገልግሎቱንም ከሙሉ ስብከቱ ጋር ዘግቦልናል:: /ማቴ.3/ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ምስክርነቱን ያስተማረውን ትምህርት <<በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።>> ማለቱን ገልጿል::/ዮሐ.325-36/:: ወንጌላዊው ማርቆስም የጽድቅ ምስክር ሆኖ በሰማእትነት ማረፉን መስክሯል::/ማር.6/:: መንፈሳዊው ነገር ከመንፈሳዊው ጋር ሲተያይ የአንድ ቅዱስ ገድል ከዚህ የተለየ ይዘት የለውም:: 

          ገድለ ቅዱሳን ከልደት እስከ እረፍት እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር ሆኖ የሠራዉን ሥራ ምስክርነታቸውን የሚገልጥ መጽሐፍ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይመጣል ብሎ እንደሰበከን መጥቶ መሄዱን የመሰከሩ ቅዱሳን እንዴት እንደሰበኩ የት እንደሰበኩ ሲሰብኩ ምን እንደገጠማቸው መናገር የወንጌል ቀጣይ ክፍል መሆኑን ግብረ ሐዋርያት በግልጥ ያስረዳል:: በኢትዮጵያ የቱንም ቅዱስ ታሪክ ብንተርክ ገድል ብናነብ የምናገኝው ከሐዋርያት ሥራ /ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ/ የቀጠለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው:: እንዴት ተሰበከ በማን ተሰበከ ስንል የግድ የምንናገረው ስለ ቅዱሳኑ ነው:: አባ ሰላማ ተሰዓቱ ቅዱሳ ቅዱስ ያሬድ አባ ተክለ ሃይማኖት አባ ዜና ማርቆስ . . . የወንጌል አርበኞች ነበሩ:: ስለ እነርሱ ሳንናገር የምንሰብከው ወንጌል ከማን ያገኘነው ነው? ወንጌሉን ማን ጽፎልን? ማን ተርጉሞልን? ማን አቆይቶን? እነርሱ ያን ገድል ፈጽመው ባያስረክቡን የምናነበውን እንዴት እንረዳው ነበር? የማቴዎስን ወንጌል የጳውሎስን መልእክት ቆጥረው የሰጡን እነርሱ ናቸው:: ስለ ቅዱስ ዮሐንስ እንደምንናገረው እንናገርላቸዋለን እንደምንመሰክረው እንመሰክርላቸዋለን:: ጌታችን መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ጋር አስተያይተን ቅዱሳንን ካረፉ በኋላ እንኳ እናወሳቸው ዘንድ እንዲገባ በሁለት መንገድ አሳይቶናል:: 

                     ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከተመሰከሩ ምስክርነቶች የሚልቀው አምላኩ የመሰከረለት ምስክርነት ነው:: አንደኛ ስለ ቅዱሳን መታሰቢያ ሲያስተምር <<ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።>> በማለት የመሰከረው ነው::/ማቴ.10:41-42/:: የማይጠፋ ዋጋ ከሚያሰጡ ቅዱሳን አንዱ ቅዱስ ዮሐንስ ነው:: ነቢይ ነውና የነቢዩን ዋጋ ሽተን እንቀበለዋለን:: ጻድቅ ነውና ከጽድቁ በረከት ዋጋ ሽተን እንቀበለዋለን:: ደቀ መዝሙሩ ነውና በስሙ ጽዋ እጠጣለን:: ይህ የጌታችን ትምህርት ነውና እንይዘዋለን እንፈጽመዋለን:: ሁለተኛው ምስክርነቱ በብዙ ገድለ ቅዱሳን ማጠቃለያ ላይ እንደምናገኘው ጌታችን ስለ ቅዱሱ አባት ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ከእረፍቱ በኋላ የመሰከረለት ምስክርነት ነው:: <<እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥>> <<እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤>> /ማቴ.11:11 ዮሐ.535/:: እነዚህ ምስክርነቶች ምንጊዜም በገድለ ቅዱሳን የሚያበሩ ናቸው:: ቅድስናቸውን አገልግሎታቸውን ክብራቸውን ይናገራሉና:: አምላኩ የመሰከረለትን ምስክርነት መንፈግ ሴረኝነት ካልሆነ በቀር የተፈቀደ የታወቀ የተጻፈ ነው:: 

               በአጠቃላይ በዓላቸውን ስናከብር ስማቸውን ስንጠራ መታሰቢያቸውን ስናደርግ አናፍርም:: ከመወለዳቸው አስቀድሞ በነቢያት ስለተነገረላቸው ቅዱሳን መናገር ስህተት ካልሆነ በክብር በሃይማኖት በቅድስና ስላጠናቀቁትማ መናገር ምንኛ የተገባ ይሆን? አምላኩ ስለ መሰከረለት ቅዱስ ካልመሰከርን ለማን እንመሰክራለን? እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር እግዚአብሔር ከወዳጆቹ ከቅዱሳን ጋር ካልሆነ በቀር እንዴትስ ልንተርከው ልናወሳው ልንናገርለት እንችላለን? ስለቅዱሳን መናገር ማለት ስለ እግዚአብሔር መናገር ነው የምንለው በዚህ ምክንያት ነው:: ስለ ዘካርያስ ካህን ስናወራ የምናወራው እግዚአብሔር ያደረገለትን ነው:: ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ ስንመሰክር የምንመሰክረውም የእግዚአብሔር ያደረገላትን ድንቅ ሥራ ነው:: ስለ ዮሐንስ መጥምቅም መጻፍ ስለ ጌታችን መጻፍ ነው:: ነቢዩ ከእርሱ የተለየ ሕይወት የለውምና ስለ ቅዱሳን ሁሉ ስንናገር ስለ እግዚአብሔር እንናገራለን:: ቅዱስ ጳውሎስ <<መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።>> እንዲል:: /1ቆሮ.2:13/:: መስለውና አህለውት የተወለዱ አዋልድ መጻሕፍትን ከመንፈሳዊው መጽሐፍ ጋር :: አርአያቸውን ተከትለው የተጓዙ ቅዱሳንን ከቅዱሳን ጋር አስተያይተን እንጂ ይህ የሰው ጥበብ አለመሆኑን የመጥምቁ ዮሐንስ ሕይወት ምስክር ሆኖናል:: ልደቱን ምክንያት አድርገን የጻፍነው ይህ ቃል ስለ ማን ይናገራል? መንፈሳዊውን ከመንፈሳዊ ነገር ጋር እያነጸረ የሚያወራው ስለ ማን ነው? እግዚአብሔር በመጥምቁ ዮሐንስ አድሮ የሠራውን: : እግዚአብሔር በቅዱሳን አድሮ የሚሠራውን ነው:: የመጥምቁ ዮሐንስ ረድኤትና በረከት አይለየን:: አሜን::

4 comments:

  1. zemenun mewajet malet endih new !!
    EGZIABHER EJIHIN YABERTA,YEABATOCHIN MISTIRN YEGELETE MENFES KIDUS YANTEM YIGLETLH!!!!

    ReplyDelete