Thursday, September 10, 2015

ዜና ህይወቱ ለድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳስ


                   የቤተክርስቲያን የቀን መቁጠሪያን ያዘጋጀ  ድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳስ  ነው!ድሜጥሮስ ማለት መስተዋት ማለት ነው፡፡ ሀገሩ እስክንድርያ ነው፡፡ አባት እናቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋጎች ነበሩ፡፡ ላባቱ ወንድም ሴት ልጅ ነበረችው ሲሞት ልጄን ከልጅህ አትለይብኝ ብሎት አብሮ አሳድጓቸዋል፡፡አካለ መጠን ሲያደርሱ ዘመኑ አረማውያን የበዙበት አማንያን ያነሱበት ነበርና ከሌላ ብናጋባቸው ከሃይማኖት ከገቢረ ሠናይ ይርቃሉ፤ ሕገ ነፍስ ከሚፈርስ ሕገ ሥጋ ይፍረስ ብለው አጋቧቸው፡፡ በልተው ከጠገቡ ጠጥተው ከረኩ በኋላ ሥርዓተ መርዓዊ ወመርዓት ያድርሱ ብለው መጋረጃ ጣሉባቸው፡፡ እሷ አስቀድማ ድሜጥሮስ ያንተ ወንድምነት ለኔ የእኔ እኅትነት ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አለችው፡፡ እኔስ የአባት የእናቴን ፈቃድ ልፈጽም ብዬ እንጂ ፈቃዴ አይደለም፤ በዚያውስ ላይ አንቺ ከፈቀድሽ ብንተወው እንችል የለምን? አላት እንተወው አለችው፡፡ እንኪያስ አንቺንም ለሌላ እኔንም ለሌላ እንዳያጋቡን መስለን እንኑር አላት፡፡ በዚህ ተስማምተው አንድ ምንጣፍ እያነጠፉ አንድ ዐጽፍ እየተገናጸፉ 48 ዘመን ኖሩ ፡፡ ምነውመኑ ይክል ሐቁረ. እሳት በሕጽኑ ይል የለምን እንደምን ይቻላል? ቢሉ ሕሩይ ለንጽሕና ነውና አንድም እሳቱን እንዲታፈኑ ማድረግ ለጌታ ይሳነዋልን? መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ቀኝ ክንፉን ለርሱ ግራ ክንፉን ለርሷ አልብሶ አድሮ ሲነጋ በአምሳለ ርግብ በመስኮት ወጥቶ ሲሄድ ያዩት ነበር፡፡