Tuesday, September 11, 2012

ዘመኑን ዋጁ

    የተወደዳችሁ ምእመናን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገራችሁ
            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ምእመናን መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከገለጠላቸው በኋላ አያይዞ እንዴት መኖር እንዳለባቸው መክሮአቸዋል፡፡ ስለመጪው ጊዜ ሲነግራቸው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና›› ብሏቸዋል፡፡

ዘመነ ሰላም  ያድርግልን  2005

እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲመክራቸው ደግሞ ‹‹እንደጥበበኞች›› በጥበብ መመላለስ እንደሚገባቸው፤ ዳግመኛም ‹‹በጥንቃቄ›› እና ‹‹በመጠበቅ›› እየኖሩ ዘመኑን እንዲዋጁ አሳስቧቸዋል፡፡ (ኤፌ5.15-16) እነዚህ ቁም ነገሮች ለጊዜው በኤፌሶን ላሉ ምእመናን ቢጻፉም ለሁላችን ምክር እና እዝናት የሚሆኑ ናቸውና በየተ
እንመለከታቸዋለን

      ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለት ምን ማለት ነው? የቀን ክፉ አለን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ክፋት አስቦና ፈቅዶ በሚበድል በሰው ልጅ ዘንድ እንጂ በቀናት ዘንድ ክፋት የለም፡፡ ዕለታትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነው›› (1ጢሞ4.4) ስለዚህ ዕለታት በሙሉ በተፈጥሮ አንድ ናቸው፤ እንዲሁም ሁሉም መልካም ናቸው፡፡ 
የዕለታት መልካቸው የሰው ልጅ ምግባር ነው፡፡ የሰው ሥራ ክፉ የሆነ እንደሆነ ዕለታትም ይከፋሉ፡፡ ሰው መልካም ሲሆን ዘመናቱ መልካም ይሆኑለታል፡፡ ሐዋርያው በዕለት አንጻር የሰውን ክፉነት ሲነግረን ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች›› ናቸው አለን፡፡ በጸሎተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹እግዚኦ አድኅነነ እምዕለት እኪት ወባልሃነ እምኩሉ መንሱት›› - ‹‹አቤቱ ከክፉ ቀን ከፈተናም ሁሉ ፈጽመህ አድነን፡፡›› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ አበው ካህናት ሲያሳርጉ ‹‹ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!›› የሚሉት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላት መሠረት አድርገው ነው፡፡ የሰው ልጅ ምግባር ሲከፋ ዘመናቱ ክፉዎች የሚሆኑት ዕለታት የተፈጠሩት ለሰው ልጆች ጥቅም ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም›› እንዲል፡፡ (ማር2.27) ሐዋርያውም ቀኖች ለሰው የተፈጠሩ መሆናቸውን በሚጠቁም ቃል ‹‹ቀኖቹማለቱን ልብ እንበል፡፡ ‹‹ቀኖቹ›› ያለው የሰው ልጅ ቀኖች ለማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ዕለታት ለሰው ልጅ መጠቀሚያነት እስከተፈጠሩ ድረስ ሰው ሲያበላሻቸው ይበላሻሉ ማለት ነው፡፡ ሰው ምግባሩን ሲያከፋ ዕለታት እየከፉ የሚሄዱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሰው መልካም ሲሁንም ‹‹ቀኖቹ›› መልካም ይሆኑለታል፡፡
                                   መጪው ጊዜ
      ነቢዩ ዳንኤል እንደተናገረው ዘመን እየገፋ በሄደ ቁጥር ዕውቀት ይበዛል፡፡ ሥልጣኔም ይሰፋል፡፡ (ዳን12.4) ይሁን እንጂ በሥነ ምግባር ደረጃ የሰው ልጆች ክፋት እየጨመረና በምድር ላይ ኃጢአት በምልዓት እየተፈጸመ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ይህን እውነት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለቱ የሚገባ ነው፡፡
አምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነገር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዘመናት እምነት በሰው ልጅ ዘንድ ጎደሎ እንደሚሆን በተጠየቅ መንገድ ‹‹ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ሉቃ18.8) እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡›› በማለት ከነምክንያቱ አስቀምጦልናል፡፡ (ማቴ24.12) ይህ በግልጥ የሚታይ እውነት ስለሆነ ምስክርም አያስፈልገውም፡፡ እንግዲህ በመጪዎቹ ዘመናት እምነትና ፍቅር በሰው መሃል ካልተገኙ የሰው ልጅ ለበጎ ምግባር ምን መነሻ ይኖረዋል? ከፍቅርስ የሚበልጥ ምን ምግባር ይኖረዋል? እንዲህስ ከሆነ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› መባሉ ተገቢ አይደለምን?
      ቀኖቹ ክፉዎች መሆናቸው እና የሰው ልጆች መንፈሳዊ ደረጃ እየዘቀጠ የሚሄድ መሆኑን ከራሳችን የግል ሕይወት በመነሣት መረዳት የምንችለው ነው፡፡ አብዛኞቻችን ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ትጋት ስንጀምር እንዳነበረን አይሆንልንም፡፡ መንፈሳዊ ኑሮ ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል እንደሚባለው እየሆነብን የምንቸገር ብዙዎች ነን፡፡ ስንጀምር የነበረን ለጸሎት ማልዶ መነሣት፣ ዘወትር ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ በሱባኤ ወራት ወደገዳማት ሄዶ ደጅ መጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በመመሰጥና በድስታ ማዳመጥ፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠንቀቅ፣ ንስሐ መግባት፣ ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ ወይም ከመንፈሳዎ ምሥጢራት ስለ መራቃችን መቆጨት ከውስጣችን ሙጥጥ ብሎ ያለ ይመስላል፡፡ በምትኩ ተስፋ መቁረጥ፣ ድንዛዜ ስንፍና እና ልዩ ልዩ የኃጢአት ልምምዶች ልባችንን አጣበውታል፡፡ ታዲያ በእኛ ውስጥ የምንመለከተው ይህ ሁኔታ በብዙ ሰዎች ዘንድ መኖሩን በተደጋጋሚ ስንሰማ ዘመኑ እየከፋ መምጣቱን አይነግረንምን?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› በማለት ብቻ አላበቃም፡፡ በሌላ ክፍል ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ፡፡›› እያለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከነምክንያቱ ጽፏል፡፡ (2ጢሞ3.1) መጪው ጊዜ አስጨናቂ የሚሆነው ሰዎች ‹‹ራሳቸውን የሚውዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ቅደስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ›› ሰለሚሆኑ እንደሆነ አያይዞ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው የቀኖቹን ክፉነት ብቻ ሳይሆን እኛ ከዚህ ሁሉ ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠቁሟልና ያንን ቀጥለን እንመለከታልን፡፡ 
                   1. ዘመኑን መዋጀት
ሐዋርያው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ብሎናል፡፡ ዘመንን መዋጀት ማለት ምን ማለት ነው ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመኑን መግዛት፣ ድል ማድረግ፣ ማሸነፍ፣ የራስ ማድረግ፣ ዘመኑን መቅደም እንጂ በዘመን አለመቀደምወዘተ ማለት ነው፡፡ዘመን ዘመናት የሚባሉት የሚመጡት አዳዲስ ዓመታት ብቻ አይደሉም፡፡ ያለፈውም ጊዜ የዘመን አካል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመንን መዋጀት ስለሚመጣው ብቻ ሳይሆን ስላለፈውም መመርመር፣ ታሪክን በሚገባ ማወቅ፣ ካለፈው መማርና ለወደፊቱ መጠንቀቅ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ካልመረመርነው ዘመንን ዋጀን አይባልም፡፡ የሚመጣውን ብንዋጅ ያለፈውን ዘመን ካልዋጀን ዘመኑን ዋጀን ሊባል አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመን ያፈራውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማወቅና መጠቀም ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም የሚሰፋ ሐሳብ ያለው ነው፡፡  
          ዘመኑን መዋጀት ማለት በእያንዳንዱ ቀን ፈተናዎችን እንደየአመጣጣቸው እየለዩ መመከት ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ጥንተ ጠላት ሰይጣን ዓለምን ማርኮ ለመግዛት ብዙ አሳሳች መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ አዳምንና ሔዋንን የፈተነው አምላክነትን እንዲመኙና ዕፀ በለስን እንዲበሉ በማድረግ ነው፡፡ ኢዮብን የፈተነው ያለውን ሁሉ በማውደም እና በሽታ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ነው፡፡ እስራኤልን የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ ስቧቸዋል፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ የፈተናው መንገድ ግን ከተዘረዘሩት በእጅጉ ይለያል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የሚፈትነን እንደዘመናችን ስለሆነ ዘመኑን ካልዋጀን ፈተናውን ማለፍ አንችልም፡፡ስለዚህ ሐዋርያው እንደመከረን ‹‹መጠንቀቅና›› ራሳችንን ‹‹መጠበቅ›› አለብን፡፡ ‹‹መጠንቀቅ›› ካላወቅነው፤ ነገር ግን ሊሆን ይችላል ብለን ከምንገምተው ክፉ ነገር ሁሉ ራስን ለማዳን መሽቀዳደም ሲሆን ‹‹መጠበቅ›› ደግሞ ክፉ መሆኑን ከተረዳነው ነገር ሁሉ እንዳይጎዳን የምናደርገውን ጥረት ያመለክታል፡፡ (ኤፌ55) 
                     2. በጥበብ መመላለስ
ጥበብ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይመደባል፡፡ ወይም በቅዱስ ያዕቆብ ገለጻ መሠረት ሰማያዊ እና ምድራዊ ጥበብ ይባላል፡፡ (ያዕ3.15-17) የመንፈሳዊ ጥበብ መነሻው ሃይማኖት ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ይላልና፡፡ (መዝ1)00) እግዚአብሔርን መፍራት ደግሞ በሃይማኖት ይተረጎማል፡፡ ምክንያቱም በዓይነ ሥጋ ያላዩትን እግዚአብሔርን ኃጢአት ብሠራ ይፈርድብኛል ብሎ መፍራት ራሱ ሃይማኖት ነውና፡፡ ስለዚህ የጥበብ መጀመሪያ ሃይማኖት መሆኑን በዚህ እናውቃለን፡፡ እንዲህ ከሆነ በጥበብ መመላለስ ማለት ደግሞ በሃይማኖት መመላለስ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም በጥበብ መመላለስ ማለት በዚህች ዓለም ማታለልና ክፉ አሠራር እንዳይያዙ በዘዴ፣ በዕውቀት፣ በማስተዋል፣ በብልሃትና በፈሊጥ መመላለስ ማለት ነው፡፡
በሃይማኖት መመላለስ ከክፉ ሁሉ ይሰውራል፡፡ እውነተኛ የልብ እምነት ክፉውን ሁሉ ይመክታል፡፡ ‹‹ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ ሃይማኖት ያለው ሰው በምንም በማንም አይሸነፍም፡፡ (1ዮሐ54) ስለዚህ በዚህ ዘመን ሃይማኖታችንን ጠበቅ አድርገን መያዛችን ለአሸናፊነታችን ዋስትና ነው፡፡
                        3. ከክፉ መሸሽ     
      አብዛኞቻችን በጎ ዘመን ላይ ደርሰን በሰላምና በደስታ ለመኖር የምንጓጓውን ያህል ለዚህ የሚያበቃውን መስፈርት ግን ለማሟላት ስንደክም አንገኝም፡፡ ወደፊት በመልካም ለመኖር የሚጠበቅብን ነገር አለ፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ልብ እንበል፡፡ አስቀድሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወደድ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መቼም ለዚህ ጥያቄ እኔ እፈልጋለው ብሎ መልስ የማይሰጥ አይኖርም፡፡ ቀጥሎ ማሟላት የሚገባን ነገር መኖሩን ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፡፡ ከንፈሮችህም ሽንገላን ሽንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም›› ሲል ይጠቁመናል፡፡ (መዝ33.12-14) ስለዚህ በአጭሩ ከክፉ መሸሽና መልካም ማድረግ የወደፊት መንገዳችንን እና መጪውን ዘመን ብሩህ ያደርግልናል፡፡ መልካም አኗኗር ከውስጣችን የሚፈልቅ እንጂ በግዢ የሚገኝ ቁስ አይደለምና፡፡ ደስተኛና ሰላማዊ ኑሮ መኖር ከፈለግን ምግባራችንን እናስተካክል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን?›› ብሎአልና፡፡ (ዘፍ4.7) መልካም ከሠራን ፊታችን ይበራል፡፡ ዘመኑም መልካም ይሆንልናል፡፡ እንጂ መልካም አዲስ አመት ስለተባባልን ብቻ ዘመኑ መልካም እንደማይሆንልን እንረዳ! በጎ መመኘታችን እንደተጠበቀ ሆኑ በጎ ለመሥራት አሁኑኑ እንነሣ!

                  ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን! አሜን
                          መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን
                          ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

2 comments: