Thursday, May 10, 2012

ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ይመለከታታልን?


        ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ይመለከታታልን ክፍል አራት  

     ከላይ በተነሳው ጥያቄ ላይ እስከ ክፍልሶስት ድረስ በተከታታይ ምላሽ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል በዚህ ጽሑፋችንም ቀጣዩን ክፍልይዘንላችሁ ቀርበናል እግዚአብሔር አምላክበማስተዋል ማንበቡን ያድለን አሜን
  በቀደሙት ጽሁፎቻችን እመቤታችን የውርስ ኃጥአት እንደማይመለከታት  ከብዙ በጥቂቱ ለመመልከት ሞክረናል በዛሬው ጽሑፋችን ድንግልማርያም የውርስኃጢአት ይመለከታታል  ማለት  በመሰረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ላይ የሚያስነሳቸውን ተቃርኖዎች ለመመልከት እንሞክራለን ።

   ፩. የድንግል ማርያም ሥጋ የውርስ ኃጢአት ወይም የጥንተ አብሶ ፍዳ አለበት ከተባለ  ክርስቶስ ከርሷ ሲወለድ ኃጢአት የወረሰውን ሥጋ ወሰደ ሊባል ነው  ይህ ማለት ደግሞ  በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ትምህርት ነው ምክንያቱም ለኢየሱስ ክርስቶስ ባሕሪይ ኃጢአት ፈጽሞ  አይስማማውምና ኃጢአት የነካውን ሥጋ ተዋሐደ  ከተባለ መለኮት ኃጢአት ይስማማዋል እንደማለት ነው ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ክህደት ነው ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች መመልከት ይቻላል 
«ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞት የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ» ዕብ ፯፤፳፮
           «ከኃጢአት  በቀር በነገር ሁሉ እንደኛ ተፈተነ…………» ዕብ ፬፤፲፭
             «ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን  ስለኛ ኃጢአት …………»፪ቆሮ፭፤፳
፪. የድንግል ማርያም ሥጋ የጥንተ አብሶ ፍዳ ወይም የውርስ ኃጢአት  አለበት ማለት የክርስቶስን የማዳን ስራ  አለመቀበል ነው ።    ምክንያቱንም ከዚህ እንደሚከተለው ማብራራት ይቻላል ። ጌታ ከድንግል ማርያም መርገም ያለበትን ሥጋ ከነሳ ክብር ምስጋና ይግባውና  መርገም ባለበት ሥጋ መርገምን አራቀ ማለት በጭራሽ አያስኬድም። ይህ ደግሞ አለም እንዲድን የአምላክ መውረድ መወለድ ያስፈለገበትም ምክንያት ከንቱ ሊሆን ነው ። የአምላክ መውረድ መወለድ ያስፈለገበት ምክንያትኮ ሰው  ሁሉ የመረገም የእዳ የበደል ተጠያቂ ስለነበር ንጹሕ የሚያድን በመጥፋቱ ነው።ለዚህም ነው በነብዩ ኢሳያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው
     «እግዚአብሔር አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድም  እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም ስለዚህም የገዛ ክንዱ መድኃኒትን አመጣለት ጽድቁምአገዘው» ኢሳ፶፱፡፲፮     
           አዎን እግዚአብሔር ያጣው ንጹሕ ሆኖ ስለ ሌላው የሚማልድ ካሳ ቤዛ የሚሆን ሰው ነበር ነገር ግን ሁሉ ከእዳ ከበደል በታች ስለነበሩ ንጹሕ መረገም የሌለበት ጠፋ ስለዚህም በንጹሐ ባህሪው ጌታ ንጹሕ ስጋን ተዋህዶ  ወደ እኛ መጣ ።ነብዩ የገዛ ክንዱ መድኃኒትን አመጣለት ማለቱ  እርሱ እራሱ ሰው ሆኖ አዳነን ማለቱ ነው ።  እርሱ በባህሪው ኃጢአት ስለማይስማማው  ኃጢአት የሌለበትን ሥጋ ለመዋሐዱ ምንም ሊያከራክር አይችልም ።መርገም ያለበት መርገም ያለበትን ማዳን ቢችል ኖሮ ከብዙ ነብያት አንዳቸው አለምን  ማዳን በተቻላቸው ነበር። የድንግል ማርያምን ንጽህና በጥቃቄ ከተረዳን ነገረ ድኅነትን እንዳናፋልስ ይረዳናል ለዚህም ነው ቅዱስ አትናትዮስ ሐዋርያዊ ስለጌታ ሰው መሆን ሲገልጽ ስለእመቤታችን  ንጽሕና አስረግጦ የተናገረው
«ወለደት ድንግል ዘፀንሰቶ እንዘ  ኢተአምር ብእሴ በስጋ ዘፈጠሮ ለእርሱ ወወለደቶ ዘእንበለ ደነስ ወሕማም ወኢረሰስሐት በሐሪስ ሐፀነቶ ዘእንበለ ፃማ ወድካም ወአጥበቶ ዘእንበለ ድካም ወአልሐቀቶ በሕግ ዘሥጋ  ዘእንበለ  ትካዝ ።»  ሃይማኖተ አበው ዘአትናትዮስ ፳፰፡፲፱ትርጉም
     « ለተዋሕዶ የፈጠረውን ሥጋ ያለ ወንድ ዘር ያለ ኃጢአት ያለምጥ ወለደችው  የአራስነት ግብርም አላገኛትም ያለድካም ያለመታከት አሳደገችው ያለድካም አጠባችው  ለስጋ በሚገባ ሕግ ምን አበላው ምን አለብሰው ሳትል አሳደገችው»  ማብራሪያውን በቀጣዩ ጽሁፋችን እንመለከታለን  ይቆየን 
ከዚህ በፊት ያለውን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ

No comments:

Post a Comment