Saturday, May 5, 2012

«ያለ መቃብሩ የመዳን ተስፋ የላችሁም» ለምን ተባለ ? ክፍል ሁለት

         «ያለ መቃብሩ የመዳን ተስፋ የላችሁም» ለምን ተባለ ?
 "ወአልብክሙ ተስፋ ድኂን ዘእንበለ መቃብሪሁ»
                              «ያለ መቃብሩ የመዳን ተስፋ የላችሁም»        ክፍል ሁለት
          በክፍል አንድ ጽሑፋችን በአባታችን በቅዱስ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ ያለመቃብሩ የመዳን ተስፋ የላችሁም ለምን ተባለ በሚለው ጥያቄ መነሻነት የተወሰኑ ነጥቦችን ተመልክተን በይቆየን አስተላልፈን ነበር በዚህ ጽሁፋችን ቀጣዩን ክፍል እንመለከታለን እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን አሜን
ሁለቱ መነኮሳት ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ተገናኝተው ሊቀ ጳጳሱ በእንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም ከመጡበት ቦታ ታላቅነት አንጻር መጽሐፍ ቅዱሳዊየሆነአክብሮት ሰጥቶ እንደተቀበላቸው ተመልክተናል
ከዚህም በኋላ ለምን እንደመጡሲጠይቃቸው የነፍሳችንን ድኅነት ሽተን አሉት ከየት እንደመጡ ሲጠይቃቸው ደግሞቅዱስ ተክለሃይማኖት ቃል ኪዳን ከተቀበሉበት ገድል ትሩፋት ከፈጸሙበት ከታላቁገዳም መምጣታቸውን ገለጹለት ሊቀ ጳጳሱም እጅግ ተገርሞ እንዲህ በማለት መለሰላቸው
 « ወይ ሰው የነፍሱን ድኅነት ሳያውቅ ይጎዳል በማለት ጮኽ »
      ለምን? ከሊቀ ጳጳሱ ንግግር ሶስት ነገሮችን ማስተዋል እንችላለን እነዚህም
       ፩. እምነት           
            ፪. ትህትና እና       
                ፫. ምክር    ናቸው
           ፩. እምነት ሊቀ ጳጳሱ ስለ አባታችን ስለቅዱስ ተክለሃይማኖት ገድል ትሩፋት እና ስለተሰጣቸው ቃልኪዳን በሚገባ ያውቃል ማወቅ ብቻ ሳይሆን በቃል ኪዳናቸውም ይታመናል በአባታችን በቅዱስ ተክለሃይማኖት ገድል እንደተገለጸው
«ወደ መቃብርህ የሄደውን እኔ ወደ መቃብሬ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደ ቆጥርለታለሁ ……በመቃብርህ ቦታ የተቀበረውን እምርልሃለው ይህም ቃልኪዳን እንዲሆንህ ሰጥቼሃለሁ» ገተክ ፶፬፡፲-፲፪
     የሚል ልዩ የሆነ የበረከት ቃል ኪዳን እንደተሰጣቸው ስለሚያውቅና ስለሚያምን እነዚህ መነኮሳት ከዛ መምጣታቸውን በነገሩት ጊዜ በቦታው ላይ ካለው እምነት የተነሳ ተደነቀ ። እውነት ነው ልዑል እግዚአብሔር የሰው ልጆች ይድኑ ዘንድ ቸርነቱን ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ የቅዱሳኑ በረከት ነው
     -በቅዱሳኑ መቃብር ያድናል በኤልሳ መቃብር ሙት አስነስቶአል ፪ ነገስ ፲፫፡፳
       -በቅዱሳኑ ጥላ ያድናል በቅዱስ ጴጥሮስ ጥላ ፈውሷል የሐዋ ፭፡፲፭
     -በቅዱሳኑ ጨርቅ ያድናል በቅዱስ ጳውሎስ ልብስ አድኖአል የሐዋ ፲፱፡፲-፲፪
       ታድያ በአባታችን በቅዱስ ተክለሃይማኖት መቃብር እግዚአብሔር ታአምራት ቢያደርግ፤ ቢያድን እንዴት ሊያጠራጥረን ይችላል ? ይልቁንም እንደ ሊቀ ጳጳሱ በረከት ለመሳተፍ በትህትና እና በእምነት መቅረብ ይገባል እንጂ ይህ ሊቀ ጳጳስ የሚደነቅ እምነት ነበረው ጳጳስ ሆኖ ለመነኮሳቱ ያን ያህል ክብር የሰጠው ከመጡበት ቦታ ክብር አንጻር በርከቱ እንደሚደርሰው አምኖ ነው ። ይኸውም እንደ ከነናዊቷ ሴት ያለ እምነት ነው ይህቺ ሴት ከልጆች የተረፈ ፍርፋሪ ይበቃኛል እንዳለችው ሊቀ ጳጳሱም የአባታችን የቅዱስ ተክለሃይማኖት በረከት አጽማቸው ላረፈበት ቦታ የቦታው በረከት ለመነኮሳቱ የመነኮሳቱ በረከት ለኔ ይደርሰኛል ብሎ ማመን በእውነት የሚደነቅ እምነት ነው ማቴ ፲፭፡፳፯
           ከዚህም ተነስቶ ነው ሊቀ ጳጳሱ ቦታውን የነፍስ ድኅነት የሚገኝበት በማለት የገለጸው አንድ ሊካድ የማይችል ሐቅ ሰዎች ወደ ተቀደሱ ቦታዎች ሲጓዙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የነፍሳቸውን ድኅነት እያመቻቹ መሆናቸውን ማንም አያስተባብለውም በዚህም መሰረት የአባታችን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት አጽማቸው ያረፈበት ፤ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ስፍራ ከነፍስ ድኅነት ጋር ቢያያዝ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው ።
          ፪.ትህትና በሁለተኛ ደረጃ ከሊቀጳጳሱ ንግግር የምንማረው ትህትናን ነው ቅዱሳን በሁሉ ነገር ትሁታን ናቸው ከትህትናቸውም የተነሳ ምን ጊዜም ከሌሎች በረከትን ሲሹ እንመለከታለን በትህትና ዝቅ ብለው የታናናሾቻቸውን እግር እንኳን ሳይቀር ይስማሉ ሊቀጳጳሱም ያደረገው ይህንኑ ነው በትህትና የአባታችንን በረከት ፈለገ ስለዚህም ከአባታችን የቃልኪዳን ስፍራ የመጡ መነኮሳትን አከበራቸው ከአክብሮቱም የተነሳ የመጣችሁበት ገዳም የነፍስ ድኅነት የሚገኝበት ነው በማለት ተናገረ። በእርግጥም የክርስትና መሰረታዊ መገለጫው ትህትና ነው ጌታ ራሱ መምህረ ትህትና ተብሏል ጸጋ የሚገኝበት ትልቁ ትሩፋት ትህትና ነው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል
      « ለትሁታን ጸጋን ይሰጣል ትዕቢተኞችን ግን ይቃወማል» ፩ ጴጥ፭፡፭
ቅዱሳን እንኳንስ በእግዚአብሔር ሰዎች ፊት ይቅርና በኃጥአን ፊት ሳይቀር በትህትና ራሳቸውን ዝቅ ማድረጋቸው የተለመደ መጽሀፍ ቅዱሳዊ ትውፊት ነው ስለዚህ ሊቀ ጳጳሱም በትህትና መንፈስ መነኮሳቱን አክብረው በረከት ቢፈልጉ እና የአባታችንን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ገዳም የነፍስ መዳኛ የበረከት ስፍራ ቢሉ በእውነት ያለሐሰት ትክክል ነው።
         ፫. ምክር በሶስተኛ ደረጃ ከሊቀ ጳጳሱ ንግግር የምንማረው ለመነኮሳቱ ተገቢውን ምክር መስጠቱን ነው። ይህም የገዳሙን ታላቅነት ተረድተው ባዕታቸውን አጽንተው መገኘት እንዳለባቸው የሚመክርና ሌሎችም መነኮሳት ከነዚህ ተምረው ከአጽንዖተ ባዕት ይልቅ ከገዳም ገዳም በመዞር ብቻ ጊዜአቸውን እንዳያባክኑ የሚመክር አገላለጽ ነው ።አባቶቻችን ፈሊጠኞች ናቸው በሚሰሩት እና በሚናገሩት ውስጥ ሁሉ ወገኖቻቸውን ይመክራሉ ያስተምራሉ ። ሊቀ ጳጳሱም እኒህን መነኮሳት የአባታችንን ቃል ኪዳን እንዲያስተውሉ አድርጎዋቸዋል ይህም በመነኮሳቱ ንግግር ተስተውሏል ከሊቀ ጳጳሱ ንግግር የተነሣ ሲደነቁና እንዲሁም ከተመለሱ በኋላ ስለገዳሙ ታላቅነት ሲያወሩ ኖረዋል።
                                               ይቆየን
                              ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን

No comments:

Post a Comment