Saturday, August 11, 2012

መልክዐ ተክለሃማኖት

   ክፍል ሶስት  መልክዐ ተክለሃማኖት
    ሰላም ለዝክረ ስምከ በጥንተ ፊደሉ መስቀል  ስም ክቡር ወስም ልዑል። ተክለሃማኖት ማቴዎስ በዓለ ቀዳማይ ወንጌል ከመ እወድሰከ መጠነ አውሥኦተ እክል። ማዕሠረ ልሳንየ ትፍታሕ ማርያም ድንግል። 
ትርጉ  << የስምሀ መነሻ ፊደል የመስቀል ምልክት ለሆነው እና ክቡር ገናና ለሆነው ስም አጠራርህ ሰላም እላለው የወንጌል ተቀዳሚ ስም ማቴዎስ የተባልክ ተክለሃይማኖት ሆይ እንደ ችሎታዬ አመሰግንህ ዘንድ አንደበቴ ትፈታልኝ ዘንድ ድንግል ማርያምን እማልዳለሁ።  >>  
           የአባታችን የቅዱስ ተክለሃማኖት የስማቸው መነሻ ፊደል ‘’’’ የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው  የስማቸውም ትርጉም ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው ይህም በስማቸው ላይ ስመ እግዚአብሔር እንዳለ ያስረዳናል በገድላቸው እንደተጻፈው ይህንን ስም አባታችን ያገኙት የመንፈሳዊ ተጋድⶀአችው የቅርብ ረዳት በሆነው በቅዱስ ሚካኤል አማካኝነት ነው ገድ ተክ፳፰ ፤፲፪ የቀድሞ ስማቸው ፍስሐ ጽዮን ነው ትርጉሙም የጽዮን የቤተክርስትያን ፤የእመቤታችን ደስታ ማለት ነው በአጠቃላይ የአባታችን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ስም የእግዚአብሄርን ክብር የሚገልጽ ልዩ መንፈሳዊ መልክዕት የያዘ ስም ነው።ስለስማቸው ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን መጽሐፍ ቅዱስ ስለቅዱሳን ስም ምን እንደሚል አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት
      . በቅዱሳን ስም ላይ የእግዚአብሔር ስም ይከብራል
          « በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት»ዘጸ፳፫፤፳፩
     .የቅዱሳን ስም ከስም ሁሉ የሚበልጥ ነው
          «……..ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ መታሰቢያ ስም ………» ኢሳ፶፮፤፭
      .የቅዱሳን ስም ዘላለማዊ እና የማይጠፋ ነው
          «የማይጠፋም ዘላለማዊ ስም እሰጣቸዋለሁ» ኢሳ፶፮፤፮
      . በቅዱሳን ስም የእግዚአብሔር ቤት እና ቅጽሩ በመታሰቢያነት ይሰየማል
        «በቤቴ እና በቅጽሬ ውስጥ……. የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» ኢሳ፶፮፤፭
      . በሰማያዊት ቤተ መቅደስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቀጥሎ የቅዱሳኑ ስም ተጽፎአል
     «በእነርሱም የአስራ ሁለቱ የበጉ ሃዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር» ራእይ፳፩፤፲፬
      . በቅዱሳን ስም ዝክር ማዘከር በጎ ሰራ መስራት ሰማያዊ ዋጋ አለው
          «ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው  አይጠፋባትም » ማቴ፲፤፵፪
እንግዲህ የቅዱሳኑ ስም ይህን ያህል የከበረ ከሆነ ለከበረው ስማቸው ሰላምታ መስጠት ምን ነውርነት አለው ? ስማቸውየእግዚአብሔር ስም የሚገለጥበት ከሆነ ለስማቸው ክብር መስጠት የእግዚአብሔርን ስም ማክበር አይደለምን ? ስማቸው በሰማያዊት ቤተ መቅደስ በክብር ከተጻፈ በስማቸው የእግዚአብሔር ቤት የሚሰየም ከሆነ ለስማቸው ክብር ሰላምታ መስጠት እንዴት ሊገርመን ይችላል ? ? በስማቸው የሚሰራ በጎ ስራ ሰማያዊ ዋጋ ካለው የቅዱሳኑን ስም በማወደስ ጸጋና በረከት አይገኝምን ? በአባታችን በቅዱስ ተክለሃይማኖት መልክዐ ጸሎታቸውም ላይ ለስማቸው ሰላምታ  እና በጸጋ ምስጋና ቢቀርብላቸውመጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያድረገ ነው ከላይ እንደተዘረዘርው እግዚአብሔር አምላክ የወዳጆቹን ክብር በስማቸው ቀርቶ በለበሱት ልብስ በረገጡት መሬት በጥላቸውስ እንኳን ሳይቀር ይገልጽ የለምን ? ቅዱስ ጳውሎስ በልብሱ እራፊ ጨርቅ ድውያንን ይፈውስ ነበር፤ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው ድውያንን ይፈውስ ነበር(የሐዋ፭፤፲፭ የሐዋ፲፱፤፲፪) ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናን በቅዱሳኑስም እግዚአብሔር ድንቅ ስራዎችን እንደሚሰራ ያምናሉ በስማቸውም የቅዱሳንን አምላክ ይማጽናሉ ስለዚህም ነው የአባታንን ስም እያነሱ መጸለይ ተግቢ መሆኑን ከመልክዐ ጸለታቸው የተመለከትነው።
        ሰላም ለስእርተ ርእስከ በኅሊና አምላክ ዘተፈቅዳ
             እንተ ቦን ግልባቤ አምሳለ ሠላስ ደቂቀ ይሁዳ።
           ተክለ ሃይማኖት ማርቅስ ጸሐፌ መንክራት ውስተ ሰሌዳ
            አበውእ ለከ እግዚኦ ዘስብሐተ ጋዳ። ህየንተ ወርቅ ወብሩር ጸዐዳ።
ትርጉም  እንደ ይሁዳ ልጆች መጎናጸፍያ ለሆኑትና የቁጥራቸው ብዛት በአምላክ ዘንድ ለሚታወቅ በራስህ ላይ ለሚገኝ የጸጉርህ  ብዛት ሰላም እላለሁ እንደ ቅዱስ ማርቆስ ድንቅ የምትሆን ወንጌልን የጻፍክና የሰበክ ተክለሐይማኖት ሆይ በወርቅ በብር ፈንታ የምስጋና እጅ መንሻ አቀርብልሃለሁ። ይህ ሰላምታ ከአባታችን ተክለ ሕዋሳት መካከል የጸጉራቸውን ክፍል የሚያወድስ ክፍል ነው  ከንባቡ እንደምንረዳው የአባታችን
የጸጉራቸው  ብዛት በአምላክ ዘንድ እንደሚታወቅ ይገልጻል ይህም እውነት ነው ጌታ በወንጌል ሲያስተምር እንኳንስ የአባታችን የእያንዳንዳችን የጸጉር ብዛት በእግዚአብሔር የተቆጠረ መሆኑን ገልጾልናል
       «የእናንተ የራሳችሁ ጸጉር ሁሉ እንኳን የተቆጠረ ነው» ሉቃ ፲፪፤፯
ስለዚህም በመልክዐ ጸሎታቸው ላይ የአባታችን የራሳቸው ጸጉር ብዛት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሚታወቅ መገለጹ ትክክል ነው ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ልዑል እግዚአብሔር በመረጣቸው ቅዱሳን በጸጉራቸውም ሳይቀር ኃይሉን እንደሚገልጽ ስለ ጸጉራቸው በተለየ ሁኔታ የተነግረላቸውን መስፍኑ ሶምሶንን እና መጥምቁ ዮሐንስን ማንሳት ሃሳቡን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል። በሶምሶን ላይ የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጸው በጸጉሩ ነበር ለዚህም ነው ሶምሶን እራሱ እንዲህ ማለት የተነገረው
       «እኔ ከናቴ ማህጸን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየው ሰው ነኝ በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም የራሴንም ጸጉር ብላጭ ኃይሌ ከኔ ይሄዳል እደክማለሁም እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ» መሳፍ ፲፮፤፲፯
አዎ ቅዱሳንን እግዚአብሔር ከማህጸን ጀምሮ ይመርጣል በተለያዩ የህዋሳት ከፍሎቻቸውም ኃይሉን ይገልጻል  አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በፈቃደ አምላክ  በብስራተ መልአክ ከማህጸን የተመረጡ ጻድቅ ናቸው ከራስ ጸጉራቸው አንስቶ መላ ህዋሳቶቻቸውን ለእግዚአብሄር የተለዩ ናቸው ስለዚህም በመላ አካላቸው ሊወደሱ ሊመሰገኑ ይገባል።
         ሌላው በዚህ ክፍል ላይ የተገለጸው አባታችን ልክ እንደ ቅዱስ ማርቆስ  ግሩም ድንቅ የምትሆን ወንጌልን እንደጻፉና እንደሰበኩ ነው። በዕርግጥም አባታችን ቅዱስ ተክለሐይማኖት ሐዲስ ሐዋርያ የወንጌል ሰባኪ ናቸው በሰው ልብ ላይ ወንጌልን ስለጻፉ የወንጌም ጸሐፊ ናቸው። ቅዱስ ተክለሃይማኖት ወንጌልን አልሰበኩም የሚል ተከራካሪ ቢነሳ ግን ገድላቸውን አንብበህ ፍረድ ከማለት ውጭ ምንም ሊባል አይቻልም።በምድረ ኢትዮጵያን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ተዘዋውረው ብዙዎችን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ የመለሱ ቅዱስ ተክለሃይማኖት አይድሉምን ? ከዚህ በላይ ወንጌልን መስበክ  አለን ? ቅዱስ ማርቆስ ከግብጽ ጣኦታት ጋራ ብዙ መከራ እየተቀበለ ተጋድሎ ወንጌልን እንደሰበከ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በአገራችን ይተለያዩ ስፍራዎች በመዟዟር ብዙ መከራ እየተቀበሉ አምልኮተ ጣኦትን እያጠፉ ወንጌልን ሰብከዋል ለዚህም ነው በወንጌላዊው በማርቆስ የተመሰሉት። የአባታችንን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ትሩፋትንና ገድልን አልመስከር  ለኢትዮጵያ ምድር ከቶ አይሆንላትም በምድሪቱ ላይ የተከተቡ የታሪክ አሻራዎች በሙሉ አባ ተክለ ሃይማኖት አባ ተክለሃይማኖት እያሉይጮሃሉና።
   ይቆየን

2 comments: